ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል መሳብ ተቻለ

ሐምሌ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል መሳቡን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ማስቻሉንና ከኮርፖሬሽኑ ጋር የውል ስምምነት እንዲፈፅሙ መደረጉን ገልጿል።

ለዚህ ውጤታማነት ኮርፖሬሽኑ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የኢንቨስትመንት የማስተዋወቅ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የቅንጅት ስራዎች እንዲሁም ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ድርሻ እንዳበረከቱ አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የውል ስምምነት የፈጸሙ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ኦፕሬሽን ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙም ጠቅሷል።

ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ የቅድመ ኦፕሬሽን ስራዎችን እያከናወኑ የሚገኙ፣ በማሽን ተከላና ሰራተኛን እያሰለጠኑ ያሉ እንዲሁም የቅድመ ኦፕሬሽን ስራዎችን አጠናቀው ወደ ምርት ሂደት የገቡ እንደሚገኙበት ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።