ከ6ሺህ ከረጢት በላይ የ “ኦ” የደም ዓይነት መሰብሰቡ ተገለጸ

የደም ባንክ የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን

ሚያዚያ 14/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በሶስት ሳምንት ውስጥ ከ6 ሺህ ከረጢት በላይ የ “ኦ” የደም ዓይነት መሰብሰቡን አስታወቀ።

የደም ባንክ አገልግሎት “ኦ” የተሰኘው የደም ዓይነት እጥረት ገጥሞት “ደም ለጋሾች ድረሱ” የሚል ጥሪ ለህብረተሰቡ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

ጥሪውን ተከትሎ በተገኘው ምላሽ አሁን ላይ ክምችቱን ወደ 15 ቀናት ከፍ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።

በብሔራዊ የደም ባንክ የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ፤ በኢትዮጵያ ካሉት የደም አይነቶች ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆነው በሳይንሳዊ አጠራሩ “ኦ” እየተባ የሚጠራው ነው።

የደም አይነቱ ለሌሎች የደም አይነት ላላቸው የሚሰጥና ለራሱ ከሌሎች የማይቀበል መሆኑ እጥረት ሊፈጠር እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ያለው ክምችት ለ15 ቀናት ብቻ ስለሆነ ልገሳው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ደም ባንኮች 340 ሺህ የደም ከረጢት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ዶክተር ተመስገን ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 257 ሺህ ከረጢት ደም 211 ሺህ ከረጢት ከለጋሾች ተሰብስቧል ነው የተባለው፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ መደፍረስ ችግር በበጀት ዓመቱ ደም ባንኮች በሙሉ አቅማቸው እንዳይንቀሳቀሱ ጫና ማሳደሩ ተጠቁሟል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

“በአዲስ አበባ ልደታ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በመገናኛ፣ ሜክሲኮ እና አራት ኪሎ አደባባዮች ላይ ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል” ያሉት ዶክተር ተመስገን፤ በክልሎች ያሉ ደም ባንኮች በበቂ ሁኔታ ከህብረተሰቡ ደም መሰብሰብ እንዲችሉ ግብአቶች ከማሟላት በተጨማሪ የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።