ከ80 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ የተወሰደ እርምጃ

አቶ ወንድአጥር መኮንን

ጳጉሜ 03/2013 (ዋልታ) ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና በህገወጥ ተግባር ውስጥ ሲሳተፉ በተገኙ ከ80 ሺህ 641 በላይ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ አቶ ወንድአጥር መኮንን እንደገለጹት፣ በህግ ማስከበር ዘመቻው እየተገኘ ያለውን ድል ለመቀልበስ በህገወጥ ተግባራት ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ የንግድ ተቋማትን በመለየት እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል፡፡

ዶላርና ምርት የደበቁ፣ ያልተገባና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሬ በማድረግ ለአሸባሪ ቡድኑ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሰረትም 80 ሺህ 641 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእገዳ፣ 520 የንግድ ድርጅቶች የንግድ ፈቃድ ስረዛ፣ 257 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእገዳ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንዳጥር፣ በ2 ሺህ 230 የንግድ ተቋማት ላይ ክስ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡

ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያትና የአቅርቦት ችግር ያልተገባ ዋጋ በመጨመር ህገ ወጥ የሆነ ገንዘብ ለማጋበስ የሚሰሩ መኖራቸውንና በተለይም የህግ ማስከበር ዘመቻ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት በዚህ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን መንግሥት አይታገስም ብለዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከመረጃና ደህንነት፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ በሚኒስትሩ የሚመራ ግብርኃይል ተዋቅሮ እየተሰራ ነው ያሉት የኮሙኒኬሽን አማካሪው፣ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡