ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ታሪክ ያለው ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት ኩባ ለኢትዮጵያ ልዩ ቦታ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በባለብዙ ፎረም ላይም ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ኩባ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ግንኙነት ለኢትዮጵያ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን በተመለከተም ለኩባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW