ካሪም ቤንዜማ የባሎን ዶር ሽልማትን አሸነፈ

ጥቅምት 8/2015 (ዋልታ) የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንና የሪያል ማድሪዱ የፊት መስመር ተጫዋች ካሪም ቤንዜማ የባሎን ዶር ሽልማትን ለመጀመሪያ ጊዜ አሸነፈ።

ፍራንስ ፉትቦል ለ66ኛ ጊዜ ባካሄደው ውድድር ካሪም ቤንዜማ የአውሮፓዊያኑ 2022 ምርጥ የወንድ እግር ኳስ ተጫዋች በመባል ነው ሽልማቱን ያሸነፈው።

ካሬም ቤንዜማ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 44 ግቦችን በማስቆጠር ሪያል ማድሪድ የስፔን ላሊጋንና ሻምፒዮንስ ሊግን እንዲያሸንፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ቤንዜማ ሽልማቱን ከአንጋፋው አግርኳስ ተጫዋችና አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን እጅ የተረከበ ሲሆን በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ቤተሰቦቹንና የቡድን አጋሮቹን አመስግኗል።

የቀድሞው የሊቨርፑል አሁን ደግሞ በባየር ሙኒክ የሚጫወተው ሳዲዮ ማኔ 2ኛ ደረጃን ሲይዝ ኬቨን ዴብሮይነና ሮበርት ሎዋንዶውስኪ የ3ኛ እና4ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሌላ በኩል የእንግሊዙ ሻምፒዮን ማንቺሰተር ሲቲ የአመቱ ምርጥ ክለብ በመባል አሸናፊ ሆኗል ።