ካፋ ዞን በአንድ ጀንበር 10 ሚሊየን ቡና ችግኝ የመትከል መርኃ-ግብር አስጀመረ

ሰኔ 7/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካፋ ዞን በአንድ ጀምበር 10 ሚሊዮን የቡና ችግኝ የመትከል መርኃ-ግብር እየተካሄደ ነው።
“የጓሮ ቡና ሽፋን የማስፋት ስትራቴጂ ዳግም ንቅናቄ” በሚል ሀሳብ በካፋ ዞን 10 ሚሊየን የቡና ችግኝ የመትከል መርኃ-ግብር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አስጀምረዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው የቡና ችግኝ ተከላ መርኃ-ግብሩ ክልሉ ያለውን እምቅ የቡና ሀብት ሽፋን ለማሳደግ የእራሱ የሆነ በጎ ሚና አለው ብለዋል።
አርሶ አደሮች ቡናን በክላስተር እንዲያለሙ በማድረግ የገበያ ትስስርና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ የጠቀሱት ም/ርዕሰ መስተዳደር ነጋሽ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን ነው ያሉት፡፡
ዞኑ በ 4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ከሚያዚያ እስከ ሀምሌ 33 ሚሊየን የችግኝ ለመትከል ያቀደ ሲሆን እስካሁንም 25 ሚሊየን ችግኝ መተከሉ ተገልጿል።
የካፋ ዞን ባለፈው ዓመት 6 ሺሕ ቶን ቡና ብቻ ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረበ ሲሆን በዘንድሮ በጀት ዓመት በእጥፍ በማሳደግ 13 ሺሕ 500 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል።
በደረሰ አማረ