ክልሉን በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት እንደሚገባ ተገለጸ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) የደበብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በዳውሮ ዞን የአመራር አቅም ግንባታ ስልጠና ሲወስዱ የቆዩ የዳውሮና ኮንታ ዞኖች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደበብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ፋጅዮ ሳፒ መሪነት የንጉስ ሀላላ የድንጋይ ካብና ኡማ ሰው ሰራሽ ሀይቅን ጎብኝተዋል።

ኃላፊው ክልሉን በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት እንደሚገባ ገልፀዋል።

አክለውም ጥንት የዳውሮ አባቶች የሰሩት የንጉስ ሀላላ የድንጋይ ካብ አሁን ላለው ትውልድ ትልቅ የጥንካሬ ማስተማሪያ እንደሆነም መናገራቸውን ከዞኑ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ምትኩ መኩሪያ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጥንት አባቶች የሰሩትን ታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችን ጠብቆና ተንከባክቦ ማቆየት የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።