ክልሉ ለሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው የሥራ ቦታዎች የሚሆኑ ከተሞችን የመለየት ሥራ እየሰራ ነው- ም/ር/መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

መጋቢት 3/2014 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ክልሉ ለሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው የሥራ ቦታዎች የሚሆኑ ከተሞችን የመለየት ሥራ እየሰራ መሆኑን ገለጹ።

በክልሉ ሕገ መንግሥት በጸደቀው መሰረት የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ብዝሃ ርዕሰ ከተሞች እንደሚኖሩት የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የጥናት ሥራው በአጭር ጊዜ ሲጠናቀቅ የክልሉ መቀመጫ ከተሞች ብዛት እና በእነዚህ ከተሞች ላይ የሚኖሩት መንግሥታዊ ተቋማት ተለይተው ወደ ሥራ ይገባሉ ብለዋል።

በክልሉ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በስሩ ባሉ ዞኖች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ እንዲሆን እንደሚያደርገውና በዛት ያላቸው ከተሞች የክልሉ መቀመጫ መሆናቸው የአገልግሎት አሰጣጡ እንዲሳለጥና በክልሉ ያሉ ሕዝቦችን በአግባቡ በመንግሥታዊ ተቋማትም ይሁን ሌሎች የፖለቲካ ሥልጣን ወንበሮች ላይ ውክልና እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች አምነውባቸው የሚደራጁ በቁጥር ከአንድ በላይ የሚሆኑ የክልል ማዕከላት እንደሚኖሩ ያመለከቱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስፈጻሚ አካላት እና ተቋማት በክልሉ ውስጥ ባሉ ዞኖች ውስጥ በተመረጡ ከተሞች ላይ የሚደለደሉ እንደሆነና ጥናቱ እስከሚጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት በቦንጋ ከተማ መቀመጫውን በማድረግ ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህ ጉዳይ በጋራ መግባባት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ውይይት እንደሚደረግበትም ገልጸዋል።

ክልሉ ከተመሰረተ ጀምሮ የመንግሥት እና የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን መወጣት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የሰው ኃይል የማሰማራት እና መደበኛ ተግባራትን ሲከውን እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥን፣ የልማት ሥራዎች እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በየዞኖች እና ወረዳዎች የማስጀመር እንዲሁም ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በጋራ የፈሩ ሀብቶችን እና እዳዎችን የመለየት ሥራ መሰራቱንም አመልክተዋል።

ክልሉ በተወሰነ መልኩ ከልማት ወደ ኋላ የቀረ በመሆኑ የመንገድ ሥራዎች፣ የጤና ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት ተደራሽነት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ ትኩረት ይደረጋልም ነው ያሉት።

ክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ያለውና ለም አካባቢ ቢሆንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና ሥራ ማከናወን የትኩረት አቅጣጫው እንደሆነ አመልክተው ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ በርካታ መሰረተ ልማቶችን ለይቶ የማጠናቀቅ ሥራም ይሰራል ብለዋል።

ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ከደቡብ ሱዳን በተለያየ መልኩ ወደ ክልሉ ሰርገው የሚገቡ የታጠቁ ኃይሎች አጎራባች ዞኖች ላይ የጸጥታ ስጋት እየፈጠሩ እንደሚገኙ አውስተው እነዚህ ሰርጎ ገብ ታጣቂዎችም የሰው ሕይወት እንደሚያጠፉ፣ የአርብቶ አደር ከብቶች እንደሚዘርፉ እና መሰል ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራዎች እንደሚያደርጉ አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር እና የክልሉን የጸጥታ ኃይል በማሰማራት ለማስቆም ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሚገኙ አመልክተው ይህንኑ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ጉዳይ ትኩረት የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመዋል።

አካባቢው የወርቅ ማዕድናት ምርት የሚካሄድበት እንደሆነና ክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል ሕገ ወጥ ንግድና የጸጥታ ስጋት ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ እና ታሪካዊ ቅርሶች ያሉበት ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ/ር) የመገናኛ ብዙኃን ክልሉ ድረስ በመምጣት በክልሉ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡