ክልሉ ላጋጠሙት ፈተናዎች እጅ ሳይሰጥ ታሪክ የሚያስታውሳቸውን ድሎች አስመዝግቧል – የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት

ነሐሴ 13/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ላጋጠሙት ፈተናዎች እጅ ሳይሰጥ ታሪክ የሚያስታውሳቸውን ድሎች እያስመዘገበ ዛሬ ላይ ደርሷል ሲል የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከ30 ዓመታት በፊት ኦሮሚያ የሚባል ክልል እንዳልነበረና በተከፈለ የሕዝቦች መሥዋዕትነት ኦሮሚያን ዕውን ማድረግ እንደተቻለ አውስቷል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ነሐሴ 13 ቀን 1984 ዓ.ም መመሥረቱንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡

መግለጫው የኦሮሞ ሕዝብ በተለያዩ ወቅቶች ያጋጠሙትን የጭቆና ቀንበሮች እና ሕዝብን ከሕዝብ የማጫረስ አጀንዳዎች በከፈለው መሥዋዕትነት እየመለሰ ዛሬ ለደረሰበት የትምህርት፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማኅበረሰብ ልማት መብቃቱን አንስቷል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ አፋን ኦሮሞ የመናገር፣ ቴክኖሎጂ የመጠቀም፣ ባሕሉን የማሳደግ እና ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት የተከለከለበት ዘመን እንደነበርም መግለጫው አስታውሷል።

ዛሬ ላይ ግን ቀድመው እንደ ጀኔራል ዋቆ ጉቱ ያሉ ጀግኖች በከፈሉት መሥዋዕትነት ሳይንስና ቴክኖሎጂን የተማረ የቁቤ ትውልድ ድርብ ድል ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄው፣ ባሕሉን፣ ቋንቋውን፣ ታሪኩንና ወጉን የማልማት መብቱና ጥቅሙን ሁሉ ማስከበር መቻሉንም ነው መግለጫው ያነሳው፡፡

ዛሬ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የሚያከብረው የትናንቱን መጥፎ ታሪክና ጠባሳ እያሰበ ሳይሆን የኢትዮጵያን ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ የስኬት መንገዶች ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን ጠንክሮ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሀገሪቱና በክልሉ የተከሰተውን የሰላምና ያለመረጋጋት ችግር ለመመለስ እንደሚተጋ መግለጹን የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽንን ጠቅሶ ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡