ክልሉ 205 ሚሊየን ኩንታል የመኸር ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) በመኸር ወቅት 2 መቶ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየሠራ እንደሆነ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለፀ፡፡

በክልሉ የበቆሎ አዘርት በክላስተር ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በምዕራብ ሸዋ ዞን ተጀምሯል፡፡

በዞኑ ኖኖ ወረዳ በሦስቱ ቀበሌዎች ማለትም ቢፍቱ ጀላላ፣ ናኖ አሎ እና ናኖ ቆንደላ ቀበሌዎች የክላስተር መርኃ ግብሩ ሲጀመር 1 ሺሕ 35 ሄክታር በቀበሌ አርሶ አደሮቹ ይለማል ተብሏል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጌቱ ገመቹ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት በመኸር ወቅቱ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆነው በክላስተር እንደሚለማ ነው የተናገሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግሥት የምርጥ ዘርና ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚታየውን ክፍተት በመቅረፍ የታቀደውን የ 2 መቶ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየሠራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በሰለሞን በየነ