ክልል አቀፍ የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽን በቦንጋ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) ክልል አቀፍ የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽን “ባህል ለዘላቂ ሠላምና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽኑ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት ነው እየተከበረ የሚገኘው።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ/ር)፣ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው፣ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ፋንታሁን ብላቴን ጨምሮ የተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 27/2014 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት ነው በቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም የሚከበረው።
በባህል ኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫል የክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ምርቶቻቸውን፣ ባህላቸውን፣ አልባሳቶቻቸውን፣ ባህላዊ ምግብና መጠጦችን ለታዳሚዎች እያስተዋውቁበት ይገኛሉ።
የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽን በተመለከተ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ እና በመርኃ ግብሩ የተለያዩ የፎቶ አውደ ርዕይ እንደሚኖ ከወጣው ፕሮግራም ለመረዳት ተችሏል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በውስጡ 13 ብሔረሰብ የያዘ ክልል መሆኑ ይታወቃል።
አድማሱ አራጋው (ከቦንጋ)