“ክብር ለሀገር አንድነትና አብሮነት ለተሠው ጀግኖች” በሚል የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – “ክብር ለሀገር አንድነትና አብሮነት ለተሠው ጀግኖች” በሚል የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

“ክብር ለሀገር አንድነትና አብሮነት ለተሠዉ ጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት አባላት” በሚል መሪ ሃሳብ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና በመዲናዋ የሚገኙ አርበኞች እንዲሁም ወጣቶች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

ለውይይቱ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ተተካ በቀለ በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ አገር ለማፍረስ እቅድ የነበረው የህወሃት ጁንታ ድል መደረጉን ገልጸዋል።

የጁንታው ሃይል ወደ መቀሌ ያፈገፈገው በዴሞክራሲያዊ ሂደት ሽንፈት ገጥሞት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህ ተስፋ በመቁረጡ አገር ለመበታተን ብዙ ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል።

“ሆኖም መንግስት ባካሄደው የህግ መስከበር ዘመቻ የጥፋት ቡድኑን እቅድ እንዳይሳካ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ የሰላም ዋስትና እና ዴሞክራሲ እውን ለማድርግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዘንድሮ በተካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ወደሚፈለገው የዴሞክራሲ አቅጣጫ ጉዞዋን እንደምትቀጥል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በወይይት መድረኩ ላይ “መከላከያችን የኢትዮጵያውያን የስነ-ልቦና ከፍታ ማሳያ ነው፣ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጋራ እንከላከል፣ የመከላከያ ሰራዊት ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ አለብን፣ ማንም ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻለውም” የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።