መስከረም 12/2015 (ዋልታ) የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለሀብቶች ለ3ኛ ዙር ያሰባሰበውን ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አስረከበ።
አስተዳደሩ ድጋፉን በሥሩ ከሚገኙ ወረዳዎች፣ ነዋሪዎች እና ባለሀብቶች ያሰባሰበ ሲሆን ለሰራዊትቱ አባላት የሚውሉ 70 ሰንጋዎች፣ 114 በግ እና ፍየሎች፣ 12 ሺሕ 500 ሸበጥ የበረሃ ጫማ፣ 13 ሺሕ 489 ቁምጣ፣ 5 ሺሕ 632 የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እና የውስጥ ልብስ እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ ግብአቶች በዛሬው እለት ወደ ግንባር መላኩን አስታውቋል፡፡
የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር ከዚህ ቀደም የክፍለ ከተማው ህብረተሰቡን በማስተባበር በገንዘብ እና አይይነት በሁለት ዙር ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ለመከላከያ ሰራዊትና ለጥምር ኃይሉ ለ3ኛ ዙር ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማስረከቡን ገልፀዋል።
የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ሀገርን ለማዳን ውድ ሕይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት ሰራዊቱን ከመቀላቀል ጀምሮ በዓይነትና በገንዘብ የሚደረገው ድጋፍ አጠናክረው በማስቀጠል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አለኝታነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውንን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ምክትል እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አለማየሁ እጅጉ ለ3ኛ ዙር የተደረገው ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚሰጠው ሞራል ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
በድጋፉ ላይ በተለያየ መልኩ አስተዋፅኦ ላበረከቱት አካላትም ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከክፍለ ከተማው ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።