ኮሚሽኑ ሌብነትና ብልሹ አሰራር በኢትዮጵያ ቁልፍ ማኅበራዊ ችግር እየሆነ ነው አለ

ሚያዝያ 2/2014 (ዋልታ) ሌብነትና ብልሹ አሰራር በኢትዮጵያ ቁልፍ ማኅበራዊ ችግር እየሆነ መምጣቱን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በኮሚሽኑ የማቴሪያል ዝግጅትና የሥነ-ምግባር ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አክሊሉ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት ሌብነት እንደ አገር የስጋት ደረጃው እየጨመረ መጥቷል፡፡

ከ6 ዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት ሙስና ከማህበራዊ ችግሮች ውስጥ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ በቅርቡ በተካሄደ ጥናት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ሶስተኛው ማኅበራዊ ችግር መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል::

ይህም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ያህል እየተባባሰ መምጣቱን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መታገል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም በኃላፊነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ተቋማት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት መገንባት ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አንስተው ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድ መፍጠር ደግሞ የችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡