ኮሚሽኑ በትምህርቱ ዘርፍ የሚታዩ የሙስናና ብልሹ አሠራርን በተመለከተ ጥናት አካሄደ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን

መስከረም 11/2015 (ዋልታ) የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በትምህርቱ ዘርፍ የሚታዩ የሙስናና ብልሹ አሠራርን በተመለከተ ጥናት ማካሄዱን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከ600 በላይ ለሚሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ የትምህርት ዘርፍ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ሥራ አስፈፃሚዎች በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

በስልጠናው ላይ ኮሚሽኑ ያስጠናው በትምህርት ሴክተሩ የሚታዩ የሙስና ስጋት ተጋላጭነት ጥናት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡

ጥናቱ የተካሄደው በትምህርት ሚኒስቴር፣ በመንግሥትና በግል ዩኒቨርሲቲዎች፣ በፈተናዎች እና ምዘና አገልግሎት፣ በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ በተመረጡ የትምህርት ተቋማት ላይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ብዛት ያላቸው የሙስና ስጋቶች መለየታቸውም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

የመምህራን በተደጋጋሚ ክፍል አለመግባት፣ ሕገወጥ ቅጥር፣ ዝውውር እና ደረጃ ዕድገት፣ የአሠራር ግልጽነት መጓደል እና ግዥዎች ሕግና ደንብን ተከትለው አለመከናወን ጥናት ከተደረገባቸው ሁሉም ተቋማት ላይ ከተገኙ ክፍተቶች መካከል ይገኙበታል ተብሏል፡፡

ጥናቱ ለሙስና እና ብልሹ አሠራር ሊጋለጡ ይችላሉ የተባሉ የሥራ ክፍሎችን መለየቱም ተጠቁሟል፡፡

ግዥ፣ ፋይናንስ፣ የሰው ሃብት ልማት እና የንብረት ክፍሎች ለሙስና የመጋለጥ ከፍተኛ ዕድል እንዳላቸው ጥናቱ ማመላከቱን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW