ኮሚሽኑ እየተጓዘበት ያለው የለውጥ መንገድ የማይናወጥ ኢኮኖሚን ለመገንባት እንደሚያግዝ ተገለጸ

መጋቢት 8/2014 (ዋልታ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ተፈሪ ፍቅሬ የተመራ የልኡካን ቡድን በጉምሩክ ኮሚሽን የተከናወኑ ሁለንተናዊ የለውጥ ሥራዎችን ተመልክቷል፡፡
ሚኒስትሩ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው ቀጣይነት ያለው አስተማማኝ ገቢ ሲኖር መሆኑን ጠቅሰው ኮሚሽኑ አሁን እየተጓዘበት ያለው የለውጥ መንገድ የማይናወጥ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
በኮሚሽኑ ምቹ የሥራ ከባቢን የመፍጠር ሳይንስ በተሟላ መልኩ መተግበሩን በጉብኝታቸው ወቅት እንደተመለከቱ የጠቆሙት ሚኒስትሩ በኮሚሽኑ እየተተገበሩ ያሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎች፣ ሰብኣዊ ልማት እና የአሰራር ማሻሻያዎች ለሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትም ጭምር ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ኮሚሽኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተሳለበትን መጥፎ ገጽታ ለመቀየር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
የኮሚሽኑ አመራሮች እና ሰራተኞችም ዘመናት በተለዋወጡ ቁጥር የማይናወጥ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
”በኮሚሽኑ የተተገበሩ ሁለንተናዊ ለውጦች በተለይም ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠር ረገድ የተሰሩት ሥራዎች ከየትኛውም ሀገር ተሞክሮ ያልተወሰዱ፣ ከለውጥ ጥማት እና ከማህበረሰቡ የለውጥ ፍላጎት የተወለደ ነው” ማለታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
በጉብኝቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአገልግሎቶች እና መልካም አስተዳደር ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሐይ ጳውሎስ እና ሌሎች የጽሕፈት ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡