ኮሚሽኑ የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሪፖርት ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ለሶስት ተከታታይ ቀናት የደረሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

በጥናቱ ከ30 በላይ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ 40 የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎችን መዳሰሳቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በክልሉ በተከሰተ የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በንጹሃን ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ የወንጀል ባሕርያትን የሚያሟሉ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ሪፖርቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ በክልሉ 123 ሰዎች ሞተዋል፣ 500 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል እንዲሁም በሺህዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቃቱ ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት እና ዘግናኝ በሚባል መልኩ መፈጸሙን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ጥቃቱ ብሔርን እና ሐይማኖትን መነሻ በማድረግ ንጹሓን ዜጎች ላይ መፈጸሙን ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ጠቁሟል፡፡

በክልሉ የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው የገጠመውን መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና የፀጥታ አባሎቹንም የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ሁኔታ በመሰማራታቸው ኃላፊነታቸው እጅግ ፈታኝ ነበር የተባለ ሲሆን፣ በተወሰኑ ቦታዎች የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑም ተነግሯል፡፡

በአንድንድ አካባቢዎች ደግሞ የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ  እርምጃ በሁከት ውስጥ ያልተገኙ ሰዎችም መገደላቸው ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የጸጥታ ኃይል አባላት በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃቶች ሲፈጸሙ እየተመለከቱ ዝም ማለታቸው እና ተጎጂዎች ህክምና ለማግኘት ሲሞክሩ በማንነታቸው ብቻ መጉላላታቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ማንነትን መነሻ በማድረግ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑ የዘር ማጥፋት ነው ሊያስብል አይችልም  ተብሎ በጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ መንግስት ማንነትን መነሻ አድርገው ጥቃቶች ሊፈጸሙባቸው የሚችሉባቸው አካባባዎች ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበትና ጥፋተኞችም ለህግ ሊቀርቡ እንደሚገባ ምክረ ሀሳቡን ሰጥተዋል፡፡

ሰኔ 22፣ 2012 ዓ.ም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተ የጸጥታ መደፍረስ የበርካቶች ህይወት ማለፉ፣ በሰዎች አካል ጉዳት መድረሱ እና ንብረታቸውም መውደሙ የሚታወስ ነው፡፡

 

(በመስከረም ቸርነት)