ኮማንድ ፖስቱ ሰላም የማረጋገጡን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

ግንቦት 24/2014 (ዋልታ) የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት የጀመረውን ሰላም የማረጋገጥ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አዲሱ የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ ገለጹ።

ሜጀር ጀነራሉ ከፍያለው አምዴ አዲሱ የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ መሆናቸውን ተከትሎ በግልገል በለስ ከተማ የትውውቅና የርክክብ መድረክ ተካሂዷል።

ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አሁን ላይ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ከመላው የኮማንድ ፖስቱ አመራርና አባላት ጋር በቁርጠኝነት እንደሚወጡ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ፀረ ሰላም ኃይሎችን መመንጠር፣ የሕዳሴ ግድቡን ሥራ ያለምንም የፀጥታ ችግር ማስቀጠል፣ በዞኑ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን መመለስ እና ሚሊሻዎችን በየአካባቢው ማደራጀት የኮማንድ ፖስቱ ተልዕኮ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በባለፉት ሦስት ወራት ወስጥ የፀጥታ ኃይሉ በጥምረት በፈፀመው ግዳጅ በመተከል ዞን ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ፀረ ሰላም ኃይሎች ላይ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱን እና በጠላት እጅ የነበሩ ቀበሌዎችን ነፃ በማውጣት አንፃራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል ብለዋል።

ቀደም ሲል የተቀናጀ ኮማንድ ፖስቱን በበላይነት ሲመሩ የነበሩት ሌተናል ጀኔራል ደስታ አብቼ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ባሳደረው ጫና ከ1 ሺሕ 700 በላይ ህገወጥ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ ጭምር በሰላም ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀላቸውን አስታውሰዋል።