ኮርፖሬሽኑ ሀገር በቀል አምራች ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ማምረት እንዲጀምሩ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

ሐምሌ 29/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሀገር በቀል አምራች ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ማምረት እንዲጀምሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ሰለሞን ገለጹ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገልፍ ኢንጎት ኤፍዜድሲ (Gulf Ingot FZC) ከተሰኘ ድርጅት ጋር የለስላሳና የውሃ ማሸጊያነት የሚያገለግሉ ጥሬ አቃዎችን ለማምረት ተስማምቷል፡፡

ድሬዳዋ በሚገኘው ኢንዱስትሪ ፓርክ በ11 ሺሕ ሜትር ስኩዬር ላይ በመከራየት የሚሰራ መሆኑ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

ድርጅቱ ጥሬ እቃዎችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ከማቅረብ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ይህም ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከማስቀረቱም በተጨማሪ በውጭ ምንዛሬ ገቢ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለመሆኑ ተነስቷል።

መቀመጫውን በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ያደረገው ገልፍ ኢንጎት ኤፍዜድሲ (Gulf Ingot FZC) የተሰኘ ድርጅት በኬንያ እና ሩዋንዳ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ነው።

የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ሰለሞን እና በገልፍ ኢንገት ኤፍዜድሲ (Gulf Ingot FZC) የቢዝነስ ልማት ሥራ አስኪያጅ እዮስያስ ኤልያስ ናቸው።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)