ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች መኖሪያ ቤቶችን ሊገነባ ነው።
ኮርፖሬሽኑ ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስችለውን ስምምነት ኮርነር ስቶን ሃውሲንግ ዲቨሎፕመንት ግሩፕ ከተሰኘው ድርጅት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዶካን ደበበ እና የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲራክ አምባዬ ፈርመዋል።
በአገሪቷ በሚገኙ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ85 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንደሚገኙና ይህም በከተሞች ላይ ጫና እየተፈጠረ መሆኑን አቶ ሳንዶካን ገልጸዋል።
በፓርኮች አካባቢ በቂ መኖሪያ ቤቶች ባለመኖራቸው ሠራተኞች እየተቸገሩ መሆኑን አንስተው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ በአግባቡ እየተካሄደ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረቱ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቁመው ባለሃብቶች ቤቶችን እያለሙ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ማቅረብ የተሻለ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ስምምነት የጥናቱ አካል መሆኑንና ውጤታማ እንደሚሆን እንደሚጠበቅም አክለዋል።
የመጀመሪያ በሆነው ስምምነት መኖሪያ ቤቶቹ ተሰርተው ሲጠናቀቁ ከ6 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲራክ አምባዬ የቤቶች ግንባታው 13 ህንጻዎችን የሚይዝና መዝናኛ ቦታዎችና አረንጓዴ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ግንባታውን በመጪው መስከረም ለመጀመር መታቀዱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በ18 ወራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በሌላ ዜና ከኮርፖሬሽኑ ሻንጂግ የተሰኘው ኩባንያ በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ መሰማራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 35 ሺህ ሠራተኞች እንደሚገኙ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።