ኮርፖሬሽኑ በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱን አስታወቀ

ሳንዶካን ደበበ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱን አስታወቀ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ የበጀት ዓመቱን አፈፃፀም በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ አፈፃፀም ሪፖርት ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ከእቅድ በላይ መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሀገራዊ ሰላምና አለመረጋጋት የኮርፖሬሽኑን ሥራ በታቀደው መሠረት እንዳይፈፀም ተግዳሮት መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው የመቀሌ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ባህር ዳር እና ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት ማምረት አለመቻላቸውን እና አዳዲስ ባለሃብቶችንም ወደ ፓርኮቹ ማስገባት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በሀገር ውስጥ ጉዳዮች የነበረው የውጭ ጣልቃ ገብነት እና የምዕራባዊያን ተጽዕኖ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአሜሪካው ቀረጥና ኮታ ነጻ ከሆነው የንግድ ችሮታ (አጎኣ) ትስስር እንድትወጣ መደረጉ ጥቂት የማይባል ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ የፈጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ለዓለም አቀፍ ንግዱ ሌላኛው ራስ ምታት መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት አስገንብቶ ወደ ሥራ ያስገባቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህን ተጽዕኖ በመቋቋም በመንግሥት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ካለፉት ዓመታት አንፃር ሲታይ የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸውንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም በወጪ ንግድ፣ የሀገር ውስጥ ገበያ አቅርቦት እና ተኪ ምርት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡

የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግብዓት እንዲያቀርቡ በማድረግ በተፈጠረው የገበያ ትስስር ከእቅድ በላይ አፈፃፀም እንደተመዘገበና በሥራ እድል ፈጠራም ከ81 ሺሕ በላይ ለሆኑ ዜጎች በበጀት ዓመቱ የሥራ እድል እንደተፈጠረ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሳንዶካን ደበበ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በእስካሁኑ ሂደት በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተገነቡት 177 የመስሪያ ቦታ መጠለያዎች መካከል 15ቱን የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ መጠለያዎችን ሳያካትት፤ ተግባር ላይ ካሉት 162 መጠለያዎች ውስጥ 136ቱን ለባለሃብቶች በውል በማስተላለፍ የምርት ምጣኔን የማስፋት ሥራን ማከናወኑም ተመላክቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃርም ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በተለያየ ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች መድረሱን በተሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በአስታርቃቸው ወልዴ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!