“ኮቪድ 19 ኢትዮጵያ ” የተሰኘው መተግበሪያ ማሻሻያ ተደረገበት

 

የኢትዮጵያ ህረተሰብ ጤና ኢንስቲቲውት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰቻለው አባይነህ

የካቲት 16/2013 (ዋልታ) – የኮቪድ 19 አለም አቀፍ ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና ያላቸውን የጤና ባለሞያዎችን አቅም ለማጎልበት ታስቦ በግንቦት 2012 ሰራ ላይ የዋለውን “ኮቪድ 19 ኢትዮጵያ ” የተሰኘው መተግበሪያ ማሻሻያ ተደርጎበት በአዲስ መልክ መቅረቡ ተገለፀ፡፡

የሞባይል መተግበሪያው ስለ ኮቪድ 19 የተደረጉ የጥናት ውጤቶችን እና በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያስችል በአዲስ መልክ የተሸሻለ ሲሆን አዲሱ የኮቪድ 19 ኢትዮጵያ የሞባይል መተግበሪያ በዋናነት የኮቪድ 19ኝን የበሽታ ቅኝትና አሰሳ፣ ህክምና፣ የላብራቶሪ አገልግሎት ፣ ብክለትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ የአደጋ ስጋት ተግባቦትና የህብረተሰብ ተሳትፎ ፣የቤት ውስጥ ልየታ እና እንክብካቤ፣ በትምህርት ቤቶች የመከላከል እና የመቆጣጠር እርምጃዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የኢትዮጵያ ህረተሰብ ጤና ኢንስቲቲውት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰቻለው አባይነህ የሰልጠና መተግበሪያውን አሰመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለውን የኮቪድ-19 በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የጤና ባለሞያዎችን በእውቀት እና በክህሎት ብቁ ለማድረግ ብሎም የሰው ሃይልን በማብቃት ምላሽ ለመሰጠት ስራን በተጠናረ መልኩ ለመስራት ያስችላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲውትና በጤና ሚኒስቴር በአዲስ መልክ የቀረበው ይህ የሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት በሚሰጠው ስልጠና ከጤና ባለሞያዎች በተጨማሪ በትምህርት ቤት የኮቪድ 19 መከላከልና መቆጣጠር ስራን ያካተተ በመሆኑ መምህራንና በትምህርት ቤቶች የሚገኙ የኮቪድ 19 መከላከልና መቆጣጠር አሰተባባሪዎች መተግበሪያውን በመጫን ስልጠናውን እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

(በህይወት አክሊሉ)