ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ደረጃ ያሰለጠናቸውን 5 ሺህ 903 ተማሪዎችን አስመረቀ

ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ደረጃ ያሰለጠናቸውን 5 ሺህ 903 ተማሪዎችን አስመርቋል።
የሁለተኛ ትዉልድ ዩኒቨርሲቲ ከሚባሉት ዉስጥ አንዱ የሆነው እና በ1999 ዓ.ም የመማር ማስተማር ተግባር የጀመረው ወለጋ ዩኒቨርሲቲ 9 የፒኤችዲ ተማሪዎችን ጨምሮ 5 ሺህ 903 ተማሪዎችን በአንደኛ እና ሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በዛሬው ዕለት አስመርቋል ።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ስብሳቢ እና የገንዘብ ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ፣ የተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ አንጋፋ ፖለቲከኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የገንዘብ ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ተመራቂ ተማሪዎች ዛሬ ትምህርት ያጠናቀቁበት ዕለት ሳይሆን መማር የሚጀምሩበት በመሆኑ ራሳቸዉን ብዙ ለመማር ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ ለሀገር እድገት እና ብልፅግና የሚጠበቅባቸውን ድርሻ በሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
(በሶሬቻ ቀበኔቻ)