ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ መሥራት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡
በአፍሪካ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች የ2014 ዓ.ም የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በቀጣይ 60 ቀናት እቅድ ዙሪያ ከሚሲዮኑ መሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የሚሲዮኖቹ አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍስሃ ያብራሩ ሲሆን መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እያንዳንዱ ሚሲዮን ጥንካሬና ክፍተቱን በመገምገም በቀጣይ ቀሪ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው በሚገባቸው ሥራዎች ላይ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት በእቅድ ከተያዙ ሥራዎች ባሻገር ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የዓለም ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ መልኩን እየቀያየረ መሆኑን በማንሳት፤ ኢትዮጵያ እያንዳንዱ እርምጃዋን ከብሔራዊ ጥቅሟ አኳያ እየመዘነች ምክንያታዊ እና የተጠና አካሄድ መከተሏ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የሚሲዮኑ መሪዎች ባነሷቸው ጥያቄዎና አስተያየቶች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡