ወንድማማችነትን በማጠናከር ሰላማዊ የጋራ ሀገር መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) “ወንድማማችነትን በማጠናከር ሰላማዊ የጋራ ሀገር መገንባት ይገባል” ሲሉ የእምነት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ሰላምን አስመልክቶ ያዘጋጀው ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ የተለያዩ እምነት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ሀይማኖትንና ፖለቲካን መሰረት አድርገው በሚነሱ የሰላም መደፍረስ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ መክረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሀይማኖት አባቶች ወንድማችነትን በማጠናከር ሰላማዊ የጋራ ሀገር ለመገንባት ያላቸው አበርክቶ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል።

አንዱ ሌላውን አክብሮ በኖረበት ሃገር ሀይማኖት የጸብ መነሻ ሊሆን አይችልም፤ የሙስሊምና የክርስቲያን አንድነትን ዛሬ መጥቶ የሚያደፈርስ አይኖርም ሰላማችንን እንዳንነጠቅ መበርታት አለብን“ ሲሉ ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ሰላም የሰው ልጆች የሕልውና መሰረት በመሆኑ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችሉ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሁሉም እምነት አባቶች በቤተክርስቲያንም ሆነ በመስጅድ ስለ ሰላም መስበክ እንዳለባቸውና ሰላም አደፍራሾችን ማውገዝና መታገል ቸል መባል እንደሌለበት አስረድተዋል።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሀመድ ኡመር ውይይቱ “በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት ባላቸው የእምነት አባቶችና የአገር ሽማሌዎች” አስተማማኝ ሰላም በከተማዋ ማስፈንን አላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ግጭት ከሚቀሰቅሱ ነገሮች በመቆጠብ ለችግሮች ሰላማዊ አማራጭን ብቻ መከተል እንደሚኖርባቸዋል አመላክተዋል።