ወደ መድረክ መመለስ እፈልጋለሁ – ድምፃዊት ቤተልሔም (አነጋግረኝ)

ድምፃዊት ቤተልሔም (አነጋግረኝ)

ወደ መድረክ መመለስ እፈልጋለሁ – ድምፃዊት ቤተልሔም (አነጋግረኝ)- አዲስ ዋልታ ቴሌቭዥንም፤ ድምፃዊቷ አዲስ ሙዚቃ ታወጣ ዘንድ አጋዥ ይሆናል፡፡

በ90ዎቹ ዘመን ላይ አንድ ተወዳጅ ዘፈን ነበር፡፡ ዘፈኑ ዛሬም ድረስ እንደአጋጣሚ የሰማነው ከሆነ ከአፋችን የማይጠፋ ብዙ ትዝታ ያለብን ድንቅ ስራ ነው፡፡

አትፍራኝ፣ አትሽሸኝ
በአንተ ያምራል አነጋግረኝ..…..

ገና ያኔ በ90ዎቹ ላይ የጂጂን ዘፈን ተጫውታ 60 ሺሕ ብር ተሸልማለች፡፡ በሰፈሯ፣ በመኖሪያ ቤቷና በሄደችበት ሁሉ ስትዘፍን የሰሟት ሁሉ አድናቆታቸውን ሳይሰስቱ ይገልፁላታል፡፡ በአዲስ አበባ ቀጨኔ አካባቢ ነው የተወለደችው፡፡ ግጥምና ዜማ ዛሬም ድረስ ትፅፋለች፡፡ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈላትን “አትፍራኝ” ዘፈንን የዘፈነች አርቲስት ናት፡፡ ከዘፈኑ ባሻገር የሙዚቃው ክሊፕም ተወዳጅነትን ማትረፉ አይረሳም፡፡ ታዲያ ስለ ዘፈኑ ድምፃዊት ቤተልሄም ስትገልፅ የትምህርት ቤት ህይወት ያለው እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ ሲሆን መነሻውም “ሰመመን” ከተሰኘው ከሲሳይ ንጉሱ መጽሐፍ መሆኑን ትገልፃለች፡፡ ሰመመን የተሰኘው መጽሐፍ በዩኒቨርስቲ የፍቅር ታሪክ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መጽሐፍ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡

ታዲያ ድምፃዊቷ በጤና እክል ሳቢያ ለረጅም ጊዜ ከመድረክ ጠፍታ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ ቀደመ ስራዋ ልትመለስ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደሞ ድምፃዊት ጄሪ (ሀሎ አዲስ አበባ) ትልቁን ድርሻ ወስዳለች፡፡ አዲስ ዋልታ ቴሌቭዥንም ድምፃዊቷ አዲስ የሙዚቃ ስራዎችን ይዛ እንድትመጣ የራሱን እገዛ ያደርጋል፡፡ ድምፃዊት ቤተልሔም ወደ ስራዋ መመለስን አስመልክቶ ከዋልታ ሾው ጋር በነበራት ቆይታ ዛሬም ድረስ ግጥምና ዜማ ለራሴ እፅፋለሁ፣ መስራት እፈልጋለሁ፣ ወደ መድረክ መመለስ እፈልጋለሁ ብላለች፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባውን ዘፈንም ውብ አድርጋ ተጫውታለች፡፡

ድምፃዊቷ ያደረገችውን ሙሉ ቆይታ ለመከታተል ቀጣዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ
https://youtu.be/E6kPiFocze0?si=UDwXBdk1r_K9IirN