ወደ ቱርክዬ የተጓዘው የኢትዮጵያ ሕይወት አድን ቡድን ተመለሰ

የካቲት 18/2015 (ዋልታ) ወደ ቱርክዬ ሪፐብሊክ ደቡባዊ ክፍል የተጓዘው የኢትዮጵያ የፍለጋ እና ሕይወት አድን ቡድን ተልዕኮውን አጠናቆ ተመለሰ።

በቅርቡ በቱርክዬ ሪፐብሊክ ደቡባዊ ክፍል የደረሰውን አሰቃቂ ርዕደ መሬትን ተከትሎ እስካሁን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የሰዎች ሕይወት ማለፉ እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከቱርክዬ ሪፐብሊክ ጋር ካላት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተነሳ ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከጤና ሚኒስቴር የተወጣጡት 27 አባላት ያሉት የፍለጋ እና ሕይወት አድን ቡድን የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት በመፈጸም ትላንት ለሊቱን ወደ ሀገራቸው በሰላም ተመልሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ላደረገው ድጋፍ የልዑካን ቡድኑ አባላት የነፍስ አድን ስራ በመስራት ላይ እያሉ የቱርክዬ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ራሲፕ ጣኢብ ኤርዶጋን በቦታው ተገኝተው ምስጋና ማቅረባቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡