ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያን የአቀባበል ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ መሰረት በመጪዎቹ የበዓል ቀናት ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የጀግና አቀባበል ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ለሚዲያ ባለሙያዎች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም በማሳወቅና የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችን በመቀልበስ የበቃ ዘመቻን በመቀላቀልና ውጤታማ ሥራ በመስራት ላይ ናቸው።

የኅልውና ዘመቻ ግንባሩን በድል የተወጡ ዳያስፖራ ጀግኖቻችንን ስንቀበል የከተማው ነዋሪ ለነዚህ ጀግኖች የአገር ልጆች አክብሮት በመስጠትና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ለዚህም በመጪዎቹ የበዓል ቀናት ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ዳያስፖራዎች አቀባበል ከቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አንስቶ በሆቴሎች፣ በትራንስፖርት አቅራቢዎች፣ በጉብኝት ስፍራዎች ለዚህ ክብረ በዓል በተለየ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አያይዘውም ወደ አገር ቤት እንደሚመጣ ከሚጠበቀው ከፍተኛ ቁጥር አንፃር የሆቴሎች የመኝታ አቅርቦት አለመመጣጠን ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ የእንግዳ ማረፊያ፣ አፓርትመንት ያላቸው ግለሰቦች በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ተቋም በመሄድ ጀግኖች እንግዶቻችንን በተገቢ መንገድ ማስተናገድ እንዲቻል ተገቢና ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ በመተመን እንዲያሳውቁና ለመኝታ አገልግሎት ምቹ የማድረግ ሥራ ከወዲሁ እንዲጀምሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።