ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የሰላም ጓድ የዲያስፖራ አባላት በእንጦጦ ፓርክ የችግኝ ተከላ አካሄዱ

የሰላም ጓድ የዲያስፖራ አባላት

ሐምሌ 13/2013 (ዋልታ) – ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የሰላም ጓድ የዲያስፖራ አባላት በእንጦጦ ፓርክ የችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡

11 አባላት ያሉት የሰላም ጓድ የዲያስፖራ አባለት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሃገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለማየትና ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሰላም ጓድ አባላቱ በ3ኛው የአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያን እናልብሳት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፋቸው ደስተኛ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ሁሌም ተሳታፊ መሆኑን ያነሱት የሰላም ጓድ አባላቱ፣ በህብረትና በአንድነት በመጠንከር ለኢትዮጵያ ልማት ላይ ከምናደርገው አስተዋፅኦ አንዱ አረንጓዴ አሻራ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ጓድ አባላቱ የኅዳሴው ግድብ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አንድነት የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም ያልታሰበው ሙሌት መሳካቱን ነው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የሰላም ጓድ የዲያስፖራ አባላት የገለፁት፡፡

ዲያስፖራው ለሃገሩ ልማት የሚያደረግው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን፣ የዲያስፖራው በኅብረት መቆም ለውጥ እያመጣ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ዲያፖራው ለኢትዮጵያ ልማት በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ተግተን እንሰራለንም ሲሉ የዳያስፖራው አባላት አክለዋል፡፡

(በምንይሉ ደስይበለው)