ወጣቱ ሠራዊቱን እንዲቀላቀል የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥሪ

ደመቀ ዘውዱ 

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) ወጣቱ በከፍተኛ ደረጃ መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥሪ አቀረቡ።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በስልጣን በቆየባቸው ዓመታት መከላከያ በአንድ ብሔር የበላይነት የተገነባ ነበር ብለዋል።

ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ይዘው ትግራይን የማልማት ሀሳብ በሚያቀነቅኑ ኀይሎች ይመራ ስለነበር መከላከያ ሠራዊትን የኢትዮጵያ ተቋም እንደሆነ አምኖ ለመቀበል አስቸጋሪ ነበርም ነው ያሉት።

ለዚህም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ክህደትም የዚሁ ውጤት ማሳያ እንደሆነ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ኮሎኔል ደመቀ የሠራዊቱን ቁመና የማስተካከል ሥራ ከተሠራ በኋላ ሀገራዊ ስሜት ያለው ተቋም እየሆነ መምጣቱን እያስተዋልን ነውም ብለዋል።

መከላከያ ሠራዊት በዚህ ጊዜ ከሌሎች የክልል እና የፌደራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በመሆን አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን እስከመጨረሻው ለማጥፋት ትልቁን ድርሻ ወስዶ እየተፋለመ እንደሆነም ገልጸዋል።