የሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው ወጣቱ እንደመሆኑ ይህ የህበረተሰብ ክፍል ከትችት እና ከፅንፈኝነት ይልቅ በምክክር እና በሙግት የሚያምን ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በየሶስት ወሩ የሚካሄድ ወጣቱን ያማከለ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
በዚህም በሀገሪቱ በሚገኙ 1 ሺህ 100 ከተሞች የሚከናወን ሲሆን በመጀመሪያው ዙር 5 ሚሊየን ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
በመጀመሪያ ዙር “የሀገረ መንግስት ግንባታ እና የወጣቶች ሚና” በሚል ርዕስ ምክክር ይካሄዳል፡፡
መድረኩ ነፃና የትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚስተናገድበት እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡
ይህ ቀጣይነት እንዳለው የተገለፀ የምክክር እና የሙግት መድረክ በምክንያት ላይ የተመሰረተ፣ በጉዳዮች ላይ ጥልቅ ዕውቀት ያለውን ወጣት ከማፍራት ባሻገር ሰላም የሰፈነባት፣ የተረጋጋች፣ የዴሞክራሲ ባህሏ ያደገና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
ወጣት ምሁራን ይሳተፋበታል የተባለው የመጀመሪያው ዙር የምክክር መድረክ የፊታችን ቅዳሜ በ4 የክልል ከተሞች ይጀመራል፡፡
(በሳሙኤል ሃጎስ)