ዋልታ ቴሌቪዥን በሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት በሀረሪ ክልል የመጀመሪያ ቅርንጫፉን ለመክፈት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

የመግባቢያ ሰነዱ በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) እና በሀረሪ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሄኖክ ሙሉነህ ተፈርሟል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ዋልታ የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ በሀረሪ ለመክፈት በመምጣቱ ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸው የሚዲያ ሥራ እንደ መንግሥት ለሚሰሩ ሥራዎች የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም ከዋልታ ጋር መልካም ግንኙነት አለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ አሁን የተደረገው ስምምነት የሕዝብ ጥያቄንና የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን በሚመለከት በቀጣይ በስፋት ለመስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሀረሪ የፍቅርና የመቻቻል ከተማ መሆኗን በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ሥራዎች ይጠብቃልም ብለዋል።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) የክልሉ መንግሥት ከሚዲያችን ጋር በጋራ ለመስራት በመስማማቱ እናመሰግናለን ብለዋል።

ሀረሪ የቅርስ፣ የባህል፣ የመቻቻልና የአብሮነት ከተማ መሆኗንም በማንሳት ይህንን የከተማዋን ገፅታ በማስተዋወቅ በተለይ ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።

በክልሉ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን በስፋት ስንደርስ ቆይተናል፤ በቀጣይም ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የኅብረ-ብሔራዊ መገለጫ ነች ስንል ሁሉንም መድረስ የሚጠበቅ በመሆኑ በቀጣይም በሀረሪ ቋንቋ የሥርጭት ሥራ የመጀመር እቅድ መኖሩንም ጠቅሰዋል።

ሀረሪ ላይ የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ ለመጀመር የተደረገው ስምምነት በሎሎች ክልሎችም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በትዕግስት ዘላለም