ዋልያዎቹ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 10፡00 ላይ የማዳጋስካር አቻውን ይገጥማል

መጋቢት 15/2013 (ዋልታ) – ዋልያዎቹ በ2022 በካሜሩን አስተጋጅነት ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 10፡00 ላይ የማዳጋስካር አቻውን ይገጥማል፡፡

የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከጫወታው በፊት በሰጡት መግለጫ፣ ቡድናቸው ባለፉት ጨዋታዎች የነበሩ ክፍተቶች በሚያርም ሁኔታ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

“በሥነ-ልቦና እና በታክቲክ ሥራዎች ላይ ሁለገብ የሆነ ዝግጅት አድርገናል” ነው ያሉት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ለጨዋታው በሁሉም ረገድ ዝግጁ እንደሆኑና ተጋጣሚዎች በሙሉ ኃይሉ የአፍሪካ ዋንጫን ለመቀላቀል ስለሚመጣ ተገቢውን ክብር ሰጥተን በጥንቃቄ መዘጋጀት እንደሚገባን ነው የሚሰማን  ብለዋል፡፡

ከአቀራረብ አንፃር ተጋጣሚ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ አጨዋወቶችን ለማየት መሞከራቸውን እና ለዛም በሚመጥን መልኩ ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋጁ እና ጨዋታውን በመልካም እንቅስቃሴ አሸንፈው ወደ አይቮሪኮስቱ ጨዋታ ለመሄድ በጥሩ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡