ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 9ኛ ዙር ተማሪዎቹን እያስመረቀ ነው

ነሀሴ1/2013(ዋልታ) – ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ቅዳሜ ነሐሴ 1 በዋናው ግቢ እና እሑድ ነሐሴ 2 በዱራሜ ግቢ በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ ትምህርት ያስተማራቸውን 3 ሺሕ 176 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።
ከተመራቂዎቹ ውስጥ 2 ሺሕ 103 ወንዶች ሲሆኑ ቀሪ 1 ሺሕ 73ቱ ሴቶች ናቸው።
ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ውስጥ ደግሞ 42ቱ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ናቸው ተብሏል።
ተማሪዎቹ በ6 ኮሌጅ ወይም ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ54 የትምህርት ዓይነቶች የሰለጠኑ ናቸው።
የምርቃት መርሃ ግብሩ የክብር እንግዳ የሆኑት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ሰላም የሰው ዘር ሁሉ የሚሻው ቢሆንም በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች እየፈተነው ነው ብለዋል።
ለእንዲህ ዓይነት ችግሮች ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች መፍትሔ አመንጪ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ከአስተሳሰብ ጀምሮ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ያሉም ሲሆን ተመራቂዎች በቀጣይ ህይወታቸው ከልዩነት ይልቅ አንድነት ላይ እንዲሰሩ ነው መልዕክት ያስተላለፉት።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሃብታሙ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስንተባበር ጠላትን እናሸንፋለን ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ዓይነተ ብዙ መስዋዕትነትን ትፈልጋለች ብለዋል። ለዚህም ተመራቂዎች የተለያዩ የማንነት ልዩነቶችን በማቻቻል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ለ5 ምሁራን የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ለመስጠት መወሰኑን ዋልታ ከዩኒቨርሲቲው ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።