“ዋጋ ያለው ውሃ” በሚል መሪ ሀሳብ የአለም የውሃ ቀን እየተከበረ ነው

መጋቢት 13 /2013 (ዋልታ) “ዋጋ ያለው ውሃ” በሚል መሪ ቃል የአለም የውሃ ቀን በዛሬው ዕለት እየተከበረ ነው።
ውሃ የእያንዳንዳችንን ሕይወት ለሚነካው ግብርና ወይንም ምግብ፣ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ፣ ለሐይል አቅርቦት፣ ለሎጅስቲክ አገልግሎት፣ ለኢኮ ቱሪዝም ለአሳ ሃብትና እጅግ ብዙ ለሆኑ ለሰው ልጆች ፍላጎት ማሟያነት ወሳኝ ሆኖ እንደሚያገለግል እሙን ነው።
ለእርሶስ ውሐ ምንድን ነው?
በየአመቱ በመጋቢት ወር ታስቦና ተከብሮ የሚውለው የውሃ ቀን ዘንድሮም ለ27ኛ ጊዜ “ዋጋ ያለው ወይም ባለ ብዙ ዋጋው ውሃ” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ እየተከበረ ነው።
የአለም የውሃ ቀን የንጹሕ ውሃ ጠቃሚነት፣ የውሃ መገኛዎች፣ የውሃ አስተዳደርና ተጠቃሚነትን የመሳሰሉ አጀንዳዎች የሚዳሰሱበት ነው።
ዘንድሮም የተባበሩት መንግስታት (ተመድ) ቀኑን አስቦ በሚያደርገው የኦን ላይን ምክክር የውሃ ልማት አጀንዳዎችን ስኬት እንደሚቃኝ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በተለይም የሃይል አቅርቦቷን በሰፊው ከምታገኝባቸው ዘርፎች አንዱና ዋናው ውሃ ነው ፣ አገሪቱ በኤሌክትሪክ ለምትጠቀምባቸው አገልግሎቶች ሃይል አቅራቢ ሆኖ ሰፊውን ድርሻ የሚወስደው ውሃ መሆኑም ይታወቃል።
የኢትዮጵያን ተጨባጭ እድገት ከሚያሳዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባር ቀደሙና መሪ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ውሃ ከሰጠን ሰፊ በረከቶች አንዱ ነው።
ይህም ውሃ በመጪው ጊዜ በሚኖረው የእያንዳንዱ ዜጋ ስኬት ላይ የውሃ አሻራ ሰፊ መሆኑን የሚያመለክት ነው።
ይህን ያህል የሕይወት አካል የሆነውን ውሃ እርሶስ እንዴት ይገልጹታል?
ተመድ በዚህ ዓመት የውሃ ቀንን ሲያከብር የውሃ ምንጮችን ዋጋ መስጠት፣ ትኩረት ለውሃ መሰረተ ልማት፣ ለውሃ አገልግሎትና ስራዎች ዋጋ መስጠት በሚሉት ጉዳዮች ላይ ምክክር ሲያካሂድ ውሃን የማህበራዊ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወሳኝ አካል አድርጎ መንቀሳቀስ ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክሩ እንደሚያተኩር ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በአለማችን በግጭት፣ በመፈናቀልና በልዩ ልዩ ችግሮች ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ንጹሕ ውሃ እንደማያገኙ መረጃዎች እንደሚያሳይ የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።