ዋፋ በትብብር ያዘጋጀው የኢትዮ-ብራዚል የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም እየተካሄደ ነው

ግንቦት 5/2016 (አዲስ ዋልታ) ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ያዘጋጀው የኢትዮ-ብራዚል የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም በሳኦ ፖውሎ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ከኢትየጵያና ብራዚል የተውጣጡ ከ250 በላይ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች እየተሳተፉ ነው።

ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ይህን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የብራዚል ኤምባሲ እንዲሁም በብራዚል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱ ተገልጿል።

ፎረሙ ለብራዚል ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን በማድረግ ረገድ ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም በግብርናና አግሮፕሮሰሲንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በጨርቃ ጨርቅና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያለውን ሰፊ ዕድል መጠቀም ያስችላል ተብሏል።

በተጨማሪም ፎረሙ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ከብራዚል አቻዎቻቸው ጋር በመጣመር እንዲሰሩ ለማስቻልና የኢትዮጵያን ምርቶች በብራዚል ገበያ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በፎረሙ ላይ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ጣፋ ቱሉ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ ፍስሐ ይታገሱ፣ የብራዚል የንግድ የኢንዱስትሪና አገልግሎት ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ማርሲዮ ኤልያስ ሮዛ እንዲሁም የሳኦ ፖውሎ ከተማ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሳሞ ቶሳቲና ሌሎች የሁለቱ አገራት የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና የድርጅት አስተዳዳሪዎች መሳተፋቸው ነው የተጠቀሰው።