ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነትና ህብረትን በማጠናከር የገጠሙን ፈተናዎችን የምንሻገርበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ባለፉት 10 ወራት በወርቅ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ድርሻ ለነበራቸው አካላት የሽልማትና የእውቅና መርሀ ግብር በተካሄደበት ወቅት ነው።
በንግግራቸውም “ከወቅቱ አገራዊ ሁኔታ አንጻር ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነትና ህብረትን በማጠናከር የገጠሙ ፈተናዎችን የምንሻገርበት ወቅት ላይ እንገኛለን” ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የገባችበት ትግል አገርን በመፈታተን ለውጥን ለማቆም ከሚደክሙ ሃይሎች ጋር መሆኑንም ተናግረዋል።
አፍራሽ ሃይሎች አቅም እና ጊዜ እንዳያገኙ ትውልዱ አገርን በማዳን ተልዕኮ የአሸናፊነት ሚናውን ሊጫወት እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅት ርብርብ ሊደረግባቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ያነሱት አቶ ደመቀ፣ አገርን የተፈታተኑ እና የከዱ ሃይሎች ላይ ህግና ስርዓት የማስከበር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የህብረተሰቡን ደህንነትና የእለት ኑሮ ለማሻሻል የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉም በመጠቆም።
ውስጣዊ አንድነትን ስብራት ውስጥ በማስገባት በዜጎች ላይ የተለያዩ ጫናዎችና ጥፋቶች እንዲካሄዱ የሞት ሽረት ትግል የሚያካሂዱ ሀይሎችን ለመመከት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ ከዳር እስከ ዳር እውነትና ፍትህን ወደ ጎን በመተው እጅ ለመጠምዘዝና ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ሃይሎች ጭምር መኖራቸውንም አንስተዋል።
ይህ ሁኔታ በዓለም ላይ በሌሎች ከታዩ ዳኝነቶች አንጻር በኢትዮጵያ ላይ ተገቢነት የሌላቸው ጫናዎች መኖራቸውን እንደሚያሳይም ተናግረዋል።
“ለፍትህ እና ለእውነት በመጮህ ባለማድመጥ የማጨናነቅና ጫና የመፍጠር እንቅስቃሴዎችን ለመሻገር የውስጥ አንድነት፣ ብርታትና ጥንካሬ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክም መተባበርን እንደሚያሳይ አስታውስው፣ “በትንንሽ አጀንዳዎች ተተብትበን ታላቋን ኢትዮጵያን የሚያሳጣ አደጋ ውስጥ እንዳንገባ ጥንቃቄ ያሻናል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሌላ አማራጭ በሌለበት የሁሉም ጥላ እና መሰባሰቢያ በሆነችው ኢትዮጵያ ጉያ በመሰባሰብ ለጠንካራ አገር ግንባታ መረባረብ ይገባል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ ማናቸውንም ጥቃቶች ለመመከት ትውልዱ በሚያኮራ ሁኔታ እየተረባረበ መሆኑንም አንስተዋል።
“ለኢትዮጵያ ከወዳጆቿ ጋር በመቆም የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በዲፕሎማሲያዊ መልክ ምላሽ ለመስጠት የመጨረሻው መስመርና ጥግ ላይ ቆመን ለማንም የማንበረከክ፣ ለእውነትና ለፍትህ ክብራችንን ጠብቀን የምንሻገር መሆናችንን እያሳየን እንገኛለን” ብለዋል።
መንግስት እነዚህን ፈተናዎች በመሻገር የሚፈለገውን ለውጥ እውን ለማድረግ በሚያስችል መልኩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“ሊያሳንሱን የሚፈልጉ ሃይሎችን በሙሉ አሳፍሮ ለመሻገር ህብረትን ማጠንከር ይገባል” ብለዋል።
“ሊሰሙን፣ እውነትን መከተል ለሚፈልጉ ሃይሎች ደግሞ እንጮሀለን ከዚህ አልፈው ለሚጋፉን ሁሉ በአንድ ላይ ተባብረን የአገራችንን ክብር እናስጠብቃለን” ብለዋል።
ለዚህ ሁሉ ጥረት ሰላምና አንድነትን መጠበቅ እንደሚገባ ገልፀው፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ችግሮችን መሻገር እንደሚገባ በአፅኖት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።