ዓለም ባንክ ለሶማሌ ክልል ከ64 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ መደበ

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ዋና ዳይሬክተር ኡስማን ዲዮን የተመራው ልዑካን ቡድን በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ዙሪያ ከክልሉ ርዕስ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባለው ሁኔታና ለድርቁ እየተሰጠ ባለው ምላሽ ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

ከምክክሩ በኋላ ዓለም ባንክ በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ድርቅ አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ 64 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መመደቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ገልፀዋል።

ከተመደበው ድጋፍ ውስጥ 38 ሚሊዮን ዶላሩ አሁን የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል፡፡

የዓለም ባንክ ላደረገው ድጋፍ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ምስጋና ማቅረባቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ኤጄንሲ መረጃ አመላክቷል።