ዓለም አቀፍ ርሃብን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት እየቀነሰ መምጣቱ የተባበሩት መንግስታትን አሳስቧል

የተባበሩት መንግስታት ባወጣው ሪፖርት በ2030 ርሃብን ለማስወገድ የተያዘው እቅድ ሊሳካ እንደማይችል ስጋቱን ያስቀምጣል።

ለግቡ አለመሳካት እንደምክንያት የተቀመጠው አሁንም በርሃብ የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ አለመቀነሱ ነው።

ረቡዕ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም ይፋ በተደረገው ያለፈው የፈረንጆች ዓመት በ2023 ጥናት መሰረት 733 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ተርበዋል።

በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ11 ሰዎች አንዱ፣ በአፍሪካ ደግሞ ከአምስት ሰዎች አንዱ ለርሃብ አደጋ ይጋለጣል።

ጥናቱን ካዘጋጁት መካከል የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ክፍል ዳይሬክተር ዴቪድ ላቦርዴ በአንዳንድ አካባቢዎች ለውጥ ቢታይም ሁኔታው በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተባባሰ እንደሄደ ተናግረዋል።

“በ2030 ርሃብን ለማጥፋት አቅደን ከጀመርንበት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከነበረው ይልቅ ዛሬ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ነን” ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም እንደ አየር ንብረት ለውጥና ቀጣናዊ ጦርነቶች ያሉ ፈተናዎች ከአስር ዓመት በፊት ከታሰበው በላይ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመራቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣዩ አስር ዓመት ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ 582 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ብዛት፣ ጦርነትና የአየር ንብረት ለውጥ ከባድ ሸክም በሆኑባት አፍሪካ ርሃብ እየጨመረ ነው ያለው ሪፖርቱ በአንጻሩ ደግሞ እስያ እምብዛም ለውጥ ያላሳየች ሲሆን የላቲን አሜሪካ ሁኔታ መሻሻሉን አመላክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት 71.5 በመቶ ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዳልቻሉም ሪፖርቱ ያሳያል።

ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ግን 6 ነጥብ 3 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ያልቻሉት።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ለምግብ ዋስትና እና ለሥነ ምግብ የገንዘብ ድጋፍ እንዲጨምር እና አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አገራት አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግ አሳስቧል።