ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ የልማት ተሳትፎን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰውሰው የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ምክትል ፕሬዝዳንትና የኮርፖሬት አገልግሎት ዲፓርትመንት ኃላፊ ጉኪ ዉ የተመራውን የልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት የተነደፉ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ፣ ፋይናንስ እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን በመክፈት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የተደረጉ ማሻሻያዎችን አድንቀዋል።

ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በብሔራዊ የገጠር ልማት እና የምግብ ዋስትና በኩል እያደረገ ያለውን ተሳትፎም አብራርተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በአይፋድ መካከል ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀውን የሥራ ግንኙነት አስታውስው ፈንዱ በአሁኑ ወቅት 240 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባቸውን ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ድጋፉን ከፍ ለማድረግ እና አዳዲስ የሀብት ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመቀየስ የልማት ተሳትፎን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW