ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር ለ58ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም ዐቀፍ የነርሶች ቀን ‘የዓለማችንን ጤና ለማረጋገጥ ነርሶችን ማብቃት፣ ትኩረት መስጠትና የነርሶችን መብት መጠበቅ’ በሚል መሪ ሀሳብ በማክበር ላይ ይገኛል፡፡
በጤናው ዘርፍ ስኬታማ ሥራዎች እንዲመዘገቡ ነርሶች አይተኬ ሚና መጫወታቸውን በመገንዘብ፤ ለነርሶች የሚሰጠው ክብር እና ቦታ በዚያው ልክ ማደግ ይኖርበታል ነው የተባለው፡፡
ነርሶች የለውጥ እና መሻሻል ድምፅ እና ጉልበት መሆናቸውን ለማሳየት ዓለም ዐቀፍ ወረርሽኞች ሲከሰቱ ፊት አውራሪ በመሆን እንዲሁም በጦር አውድማዎች ጭምር ግንባር ቀደም ተሰላፊ በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ በመሆናቸው ለአስተፆአቸው ክብርና እውቅና መስጠት እንደሚያስፈል ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበርም እንደ ሀገር ለነርሶች ሊሰጥ በሚገባው ክብር እና እውቅና ዙሪያም ፈርጀ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለፁት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ተሻገር ወርቁ በዚህ ረገድ የመንግሥት ፖሊሲን ጨምሮ የህክምና ተቋማት መዋቅር ሊቃኙ ይገባል ብለዋል፡፡
በሔብሮን ዋልታው