ዓቃቤ ህግ በምትኩ ካሳ ላይ ክስ መሰረተ

ምትኩ ካሳ

ነሐሴ 23/2014 (ዋልታ) የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር በነበሩት ምትኩ ካሳ እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ግብራበሮቻቸው ላይ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዓቃቤ ህግ በዛሬው ዕለት ክስ መስርቷል፡፡

ከተከሳሾች ውስጥም 1 አቶ ምትኩ ካሳ ጉትሌ (የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩ)፣ 2ኛ አቶ አራጋው ለማ (የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የፋይናንስ ዳይሬክተር)፣ 3ኛ አቶ የማነ ወልደማሪያም (የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዋና ዳይሬክተር የነበሩ)፣ 4ኛ ዶ/ር ዮናስ ወልደትንሳይ (የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ስራ አስኪያጅ)፣ 5ኛ አቶ ደመውዝ ኃይሉ (ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ) ፣6ኛ ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ሰላሙ (የ1ኛ ተከሳሽ የትዳር አጋር) እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በ7ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ ካሳ (የምትኩ ካሳ ልጅ)፣ 8ኛ አቶ ኢያሱ ምትኩ ካሳ (የምትኩ ካሳ ልጅ)፣ 9ኛ አቶ መብራቱ አሰፋ (የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደዴቭሎፕመንት አሶሴሸን የመጋዘን ንብረት መዝጋቢ (ሰቶር ኦፊሰር) ፣ 10ኛአቶ ገ/ሚካኤል አብረሓ (የኤልሻዳይ አሶሴሽን ሰቶር ኦፊሰርና የንብረት ክፍል ሰራተኛ) ፣ 11ኛ አቶ ዮሃንስ በላይ ተድላ፣ 12ኛ አቶ ጌቱ አስራት እና 13ኛ ወ/ሮ ሕይወት ከበደ ክስ መመስረቱ ተገልጿል፡፡

የዓቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር እንደሚያሳየው 1ኛ ተከሳሽ በቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ በአሁኑ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነርን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች በዋና እና በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ሥልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በተጨማሪም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል በ1ኛ ፣ 3ኛ፣ 6ኛ ፣ 7ኛ ፣ 8ኛ ፣ 11ኛ፣ 12ኛ፣ እና 13ኛ ተከሳሾች ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፥ በብሔራዊ ባንክ ከተወሰነው ወይም ከተፈቀደው መጠን በላይ የውጪ ምንዛሬ ይዞ መገኘት ወንጀልን ጨምሮ 1ኛ ተከሳሽ ላይ አራት ተደራራቢ ክስ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ተመስርቶበታል፡፡

ዛሬ በነበረው ችሎት 1ኛ ፣ 8ኛ ተከሳሾች (አቶ ምትኩ ካሳ እና ልጃቸው) ከሁለት ጠበቆቻቸው ጋር እና 11 ኛ ተከሳሽ ችሎት ቀርበው ማንነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ክሱ ተነቦላቸው 8ኛ ተከሳሽ የተከሰሱበት አንቀፅ ዋስትና የማይከለክላቸው በመሆኑ ጉዳያቸውን ከውጪ ሆነው እንዲከታተሉ በጠበቆቻቸው ተጠይቋል፡፡

ዐቃቤ ህግም ተቃውሞ ባለማቅረቡ ፍርድ ቤቱ 8ኛ ተከሳሽ (ኢያሱ ምትኩ ካሳ) በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ መፍቀዱን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል 1ኛ እና 11 ኛ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እስከ መስከረም 10 ዓቃቤ ህግ በመቃወሚያው ላይ እስከ መስከረም 20 አስተያየት እንዲሰጥበት በማለት በዚህም ላይ ብይን ለመስጠትና ሌሎች ተከሳሾች ሲቀርቡ ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩና የፌደራል ፖሊስ ሌሎች ተከሳሾችን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ታዝዟል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!