ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ኮምሽኑ አደነቀ

ሚያዝያ 7/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን የአፍሪካ የፖለቲካ፣ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ኮሚሽን አደነቀ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ የፖለቲካ፣ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በመውሰድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ደኅንነት ለማረጋገጥ ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ እንዲዳረስ ለማድረግ የተናጠል የግጭት ማቆም ውሳኔ ማሳለፉን አብራርተዋል።
ወደ መቀሌ ከሚደረጉ ተከታታይነት ካላቸው የእርዳታ ጫኝ አውሮፕላን በረራዎች በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ሥር በሚቀሳበሰው የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስተባባሪነት የትላንቱን ጨምሮ እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ጋር ወደ መቀሌ እየተጓዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመላ አገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱን እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙንም አንስተዋል፡፡
አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አድንቀው የተጀመሩ ሥራዎች በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጡ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡