ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን – የበጎነት ለአብሮነት ሰልጣኝ ወጣቶች

መስከረም 27/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የበጎነት ለአብሮነት ሰልጣኝ ወጣቶች ተናገሩ።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ 8ኛው ዙር “የበጎነት ለአብሮነት ማህበራዊ አገልግሎት” የወጣቶች ስልጠና መርኃ ግብር 1ሺሕ 500 ወጣቶችን ለማሰልጠን ዛሬ ተቀብሏል።

የስልጠና ማስጀመሪያ መርኃ ግብሩም በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለቀጣይ 30 ቀናት የበጎነት ለአብሮነት ማህበራዊ አገልግሎት ለመሰልጠን ጅማ ዩኒቨርሲቲ የገቡት ወጣቶች “ሀገራችን ሰላም እንድትሆንና አንድነቷ እንዲጠበቅ የበኩላችንን እንወጣለን” ብለዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ከሶዶ ከተማ የመጣው ወጣት አሸናፊ ብርሃኑ በጎነት፣ መልካምነትና መረዳዳት ከተለማመድን ለወገኖቻችን አዛኝና ደራሽ እንጂ የምንጠላላ ልንሆን አንችልም ብሏል።

ለሀገር ሰላም እና አንድነት የእኛ የወጣቶች ሚና የጎላ በመሆኑ ለሰላም እሴቶቻችን ትልቅ ቦታ ሰጥተን በመስራት በሀገራችን ዘላቂ ሰላም የበኩላችንን እንወጣለን ነው ያለው።

ሌላዋ የበጎነት ለአብሮነት ሰልጣኝ ደምበሌ አድነው ከከምባታ ጠንባሮ የመጣች ሲሆን ሀገሬ ሰላም ትሆን ዘንድ እፈልጋለሁ፤ ለዚህም ከስልጠናው በኋላ ስለ ሰላምና በጎነት የተማርኩትን እሴት እኔም አስተምራለሁ ብላለች።

በሀገሬ ሰላምና አንድነት ብሎም መተጋገዝና መተባበር እንዲኖር የተቻለኝን ለማድረግ አልሰስትም ያለችው ወጣቷ፤ በስልጠናው የተለያዩ ክህሎቶችን እንደምታገኝ ተስፋ አድርጋለች።

በመርኃ ግብሩ የሰላም ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሂሩት ዴሌቦ እንዳሉት የበጎ ፍቃድ ተግባራት ያለማንም ግፊትና አዛዥነት የሚፈጸም ሰብአዊ ተግባር ነው ብለዋል።

ለበጎነት የሚከፈል ዋጋና መንፈሳዊ ልእልናን የሚያጎናጽፍ በመሆኑም ወጣቶች ስልጠናውን ከልባችሁ በመገንዘብ ለአገራችሁ በተግባር መስራት አለባችሁ ብለዋል።

በተለይም ስልጠናው ጥርጣሬንና መከፋፈልን አስወግዶ አንድነትን ለማጠናከር እና ብሔራዊ መግባባት ለማስፈን ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ለሌሎች ወጣቶችም አርአያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ኢንጂነር ኤፍሬም ዋቅጂራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ  መርህን የሚከተል  መሆኑን አንስተው  በበጎ ፍቃድ ስልጠናውም የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባለፉት ሰባት የ”በጎነት ለአብሮነት” በጎ-ፍቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠናዎች ከ14 ሺሕ በላይ ወጣቶችን አሰልጥኗል።

በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የስራ አመራሮች፣ ከሰላም ሚኒስቴር የመጡ እንግዶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና አባገዳዎች ተገኝተዋል።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዙር 1ሺሕ 500 ወጣቶችን ተቀብሎ የሚያሰለጥን ሲሆን ከዚህ በፊት ለ7 ዙር ወጣቶችን ተቀብሎ ማስመረቁ ይታወሳል።

የሰላም ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ባለፉት ተከታታይ ዙሮች ከመላው ሃገሪቱ የተውጣጡ ከ45 ሺሕ በላይ ወጣቶችን አሰልጥኖ በተለያዩ ቦታዎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እያበረከቱ መሆኑም ተገልጿል።