ዘመናዊ የሃይቅ ዳር ከተማ ፕሮጀክት በወላይታ ዞን አበላ አባያ ሃይቅ

ታከለ ታደሰ (ፕ/ር)

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) በወላይታ ዞን አበላ አባያ ሃይቅ ላይ በሚተገበረው ዘመናዊ የሃይቅ ዳር ከተማ (Summer City) ፕሮጀክትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተደረገ።

የምክክር መድረኩ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአበላ አባያ ወረዳ የሚገኘውን እምቅ የቱሪዝም መስህብ ሥፍራዎችን ለይቶ በማልማት ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ ከሚሰሩ ተግባራት መካከል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ታከለ ታደሰ (ፕ/ር) ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በባህል ልማት ዘርፍ መስህብ ከመለየት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በወላይታና አካባቢው ማከናወን መቻሉን ተናግረው፣ ይህም ለኢትዮጵያ ብልፅግና ጉዞ ደጋፊ ነው ብለዋል፡፡

በወላይታ ዞን የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎች በታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ ጥበቃና ልማት ላይ እምቅ ሀብት እንዳለው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ ይህን ሀብት አልምቶ መጠቀም በሚቻልበት አግባብ ሰፊ ጥናትና ምርምር ሲካሄድ መቆየቱንም ገልፀዋል፡፡

በአበላ አባያ ሰመር ሲቲ ፕሮጀክትን ለማስጀመር ሰፊ ጥናት መካሄዱንና ከዚህም ባሻገር በአበላ አባያ ሃይቅ ላይ የባህር ኃይል ማሰልጠኛ አካዳሚ ለማስጀመር የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉን ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንድርያስ ጌታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ቁልፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሥራ በመስራት ለማህበረሰብ ለውጥ እየተጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዘመናዊ የሃይቅ ዳር ከተማ ፕሮጀክት

በሃይቁ ላይ ለሚካሄደው የባህር ኃይል ትምህርት የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ንድፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

በአለበል አለማየሁ