የሀረሪ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ የሰራዊቱ አባላት የአይነት ድጋፍ አደረገ

ታኅሣሥ 2/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የአይነት ድጋፍ አደረገ፡፡

ክልሉ በጦርነቱ ምክንያት ተጎድተው ድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኘው የምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል ለሚገኙ የሰራዊቱ አባላት የአይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡

በድጋፍ ርክክቡ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ ደሙን አፍስሶ እና አጥንቱን ከስክሶ ኢትዮጵያን ማፍረሰ እንደማይቻል በተግባር ያረጋገጠው ሰራዊትን መደገፍ ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የፍየሎች፣ ቴምር፣ ወተት፣ በሶና የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ሕዝቡ አንድነቱን በማጠናከር የተገኙ ድሎችን ማስቀጠልና የኅልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ ድጋፉን ማጠናከር ይገባል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ሀገርን ለማዳን እየተደረጉ ካሉ ርብርቦች ጎን ለጎንም የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል አስፈላጊ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል አዛዥ ተወካይ ኮረኔል ብርሃኑ ዘውዱ በበኩላቸው የክልሉ ሕዝብ ከዚህ ቀደምም የተጠናከረ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከፍተኛ የህክምና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጀምሮ ለሆስፒታሉ መመደቡንም አመልክተዋል፡፡ ይህም ሰራዊቱን ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

በእለቱም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጦርነቱ ምክንያት ተጎድተው በምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል የሚገኙ የሰራዊ አባላትን መጎብኘታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡