የሀገሪቱን የትራንስፖርት ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችል መግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የአገሪቱን የትራንስፖርት ስርአት ማዘመን በሚቻልበት ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር  ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ  ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ተፈራርመዋል፡፡

የጋራ ስምምነቱ ዋና ዓላማ የአገሪቱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ስርአት በቴክኖሎጂ በማዘመን ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ተደራሽነት  ያለው አገልግሎት ለሕብረተሰቡ መስጠት መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር  ሹመቴ ግዛው(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያን የሚመጠን የትራንስፖርት ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ አስተዳደሩ የዚህ ጉዞ አካል እና ለእቅዱ መሳካት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት እድል ስላገኘን ትልቅ ክብርና ሃላፊነት ይሰማናል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢመደአ ደህንነቱ የተጠበቅ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ስርዓት እንዲኖር የመረጃዎችን ሚስጥራዊነት፣ ተአማኒነት እና ተደራሽነትን ባረጋገጠ መልኩ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የትራንስፖርት ዘርፉ ለብዙ ብዝበዛ እና ህግ ወጥ ተግባር ተጋላጭ በመሆኑ ደህንነቱ የተጠበቀ የቴክኖሎጂ ስርዓት ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ለህዝባችን በሚመጠን ልክ ግልጋሎታችንን ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ መደገፍ አማራጭ የሌለው ሥራ ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር “የትራንስፖርት እና ትራፊክ አስተዳደር ስርአት” በሚል ፕሮጀክት ማዕቀፍ 5 ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካተተ፤ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የተሽከርካሪ ምዝገባ ስርአት፣ የትራፊክ ቅጣት አስተዳደር ስርአት፣ የትራፊክ አደጋ አስተዳደር ስርአት፣ እና የኦፕሬተር ምዝግባ ሲስተም ለማዘመን እየሰራ እንደሚገኝም ሚኒስቴሯ ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለትራንስፖት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር በሶፍትዌር እና አፕሊኬሽን ልማት እና ትግበራ ላይ የማማከር፣ ዳታ ማዕከልና የአዉታረ መረብ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ እንዲሁም የሚኒስቴሩን ሰራተኞች በሳይበር ደህንነት ዙሪያ  የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ስልጠናዎች የሚሰጥ ይሆናል።

ከዚህም ባሻገር እነዚህ የቴክኖሎጂ ስርዓቶች ከተተገበሩ በኋላ ተጋላጭነቶችን መፈተሽን ጨምሮ የደህነነት ኦዲት ስራዎችን እንደሚሰራ ከኢመደአ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።