የሀገራዊ ምክክሩን የሚመሩ ኮሚሽነሮች ሀገር የሰጠቻቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በፍጹም ሃቀኝነትና ትጋት ሊወጡ ይገባል ተባለ

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) የሀገራዊ ምክክሩን ለመምራት የተመረጡትም ኮሚሽነሮች ሀገር የሰጠቻቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በፍጹም ሃቀኝነትና ትጋት ሊወጡ ይገባል ሲሉ የህግ ባለሙያ ታረቀኝ አበራ ተናገሩ፡፡
እንደ ሀገር የገጠሙ ፈተናዎች ለመሻገር እና ችግሮቻችን ለመፍታት ጊዜ የለንም የሚሉት ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ ባለሙያ ታረቀኝ አበራ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለገጠማት ችግር ሁሉን አሳታፊ ምክክር ያሻል ብለዋል፡፡
ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስኬታማ ይሆን ዘንድ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት የህግ ባለሙያው ኮሚሽኑን ለመምራት የተመረጡት ኮሚሽነሮች ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው እና በታሪክ አጋጣሚ ሀገር የሰጠቻቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በፍጹም ሃቀኝነት እና ትጋት ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
እንደ ሀገር አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ እንዴት ደረስን፤ ችግሩ የቱ ጋር ነው? የሚለውን ጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራ በመስራት ለውጥ ማምጣት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
ከህገ-መንግሥቱ አወቃቀር ጀምሮ በባለፈው ሥርዓት ለሕዝብም ይሁን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታው የረባ ሚና የሌላቸው ነገር ግን የግጭት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ነቅሶ ማውጣት አንዱ የለውጥ እና የመፍትሄ አካል ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ሀገራዊ ውይይቱ ለይስሙላ የሚደረግ ሳይሆን ለውጥ እና ራዕይን ሰንቆ ሊሆን ይገባል ያሉት የህግ ባለሙያው ታረቀኝ ከዚህ ባለፈም ዶክመንት ተደርጎ ቀጣዩ ትውልድም ሊማርበት እና ሊመራበት የሚችል መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የገጠማትን ችግሮች ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር እንደ መፍትሄ ተቀምጦ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያዊያን የሚገጥሟቸውን ችግሮች በውይይት እና በእርቅ የመፍታት ልምድ አላቸው፤ ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ ነው በኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተዋቀረው፡፡
በሜሮን መስፍን