የሀገር ህልውናና ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አንፈቅድም – ኢዜማ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) ጦርነትን እያወገዝን ሰላምን ብናስቀድምም የሀገር ህልውናና ቀጣይነት ግን በፍፁም ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አንፈቅድም ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሁሌም ቢሆን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናችንን እናረጋግጣለንም ብሏል፡፡

ህወሓት በተደጋጋሚ ከሰላም በተቃራኒ እየቆመ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመከራ መዳረጉን እንደቀጠለ ነው ያለው መግለጫው የትግራይ ህዝብም እየደረሰበት ላለው መከራ ሁሉ ዋነኛ ተጠያቂው ይኸው የሕወሓት አክራሪ ቡድን ነው ብሏል፡፡

የትግራይ ህዝብ ይህን እውነት በመረዳት ለተጨማሪ መከራና ብሶት ልጆቹን እንዳይገብር እና ሀብት ንብረቱን ለእኩይ ዓላማው እንዳያውልበት በመከላከል ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በመቆም ህወሓትን በቃህ በማለት ተገድዶም ቢሆን ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ማስገደድ ይኖርበታል ብሏል፡፡

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተጀመረው ጦርነት እንዴት እንደተጀመረ እና ምን ያህል የሰላም መንገዶች ተዘግተው አሁን ለደረስንበት ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ እንደገባን የምንዘነጋው አይደለም ብሏል ፓርቲው፡፡

ኢዜማ ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግስት ከግማሽ ርቀት በላይም ቢሆን ተጉዞ ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ እንዲሰጥ አሳስቦ እንደነበር በመግለጫው አስታውሷል፡፡

የሠላም ችግራችን በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ የሚፈጠሩ መሰል ግጭቶችን ለመከላከል መቼም ቢሆን ከሰላማዊ ንግግር የሚሻል መንገድ እንደሌለ ፓርው በጽኑ እንደሚያምንም ጠቁሟል፡፡

ያም ሆኖ በተደጋጋሚ የሚቃጣብንን ትንኮሳ በመከላከል ብቻ ከልክ ያለፈ ትዕግስት ማሳየት ህዝብን ለመከራ፣ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለድቀት፣ የማኅበረሰቡን ሥነልቦናም ለቀውስ የሚዳርግ እንዳይሆን መንግሥት በቁርጠኝነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሁሉ እንዲወጣ በድጋሚ ለማሳሰብ እንወዳለን ብሏል፡፡

ተደጋጋሚ ጦርነቶች እንዳይከሰቱ ማስቆም የሚቻለው በቂ ዝግጅት አድርጎ የጥፋት ኃይሎች ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ሲቻል ብቻ መሆኑንም ገልጿል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁሌም ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራውን ያህል ሀገራችንን የሚነካ አንድነታችንን የሚያደፈርስ ጉዳይ ሲመጣ ግን በሕብረት መቆም የምንታወቅበት ታሪካችን ነው ብሏል ኢዜማ በመግለጫው።