የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በ6ኛው ምርጫ ዙሪያ የሰላም ጥሪና የአደራ መልዕክት አስተላለፈ

ሰኔ 10/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ዙሪያ የሰላም ጥሪና የአደራ መልዕክት አስተላለፈ፡፡
ምርጫና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የግጭትና ሰላም መደፍረስ መንስኤ ሆኖው መቆየታቸውን ያስታወሰው ጉባኤው በመጪው ምርጫ ይህ እንዳይከሰት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት አለበት ነው ያለው፡፡
የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለይም ወጣቱ ሰላምን ከሚያውኩ ተግባራት እራሱን እንዲቆጥብ አባታዊ ምክር አቅርበዋል፡፡
የምርጫ አስፈፃሚዎች በድምፅ አሰጣጥ፣ በድምፅ ቆጠራ እንዲሁም የቅሬታ ማቅረብ ሂደቱን ፍፁም ሰላማዊ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
የፀጥታ አካላትም በገለልተኝነት መርህ የገቡትን ቃል ኪዳን በቅንነትና በቁርጠኝነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሽንፈትን በፀጋ መቀበልንም ማሳየት እንደሚገባቸው ተጠቅሷል፡፡
የሃይማኖት መሪዎች፣ ምዕመናን ምርጫው ከሁከት የፀዳ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተማሪና አስታራቂ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
መገናኛ ብዙሃንም የህዝብና የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ ከሚጥል መረጃ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡
የአረብ ሊግ ሀገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለግብፅና ለሱዳን ያሳዩት ፍትሃዊነት የጎደለው ውግንና ኢትዮጵያዊያንን ያላከበረ ነውም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፀሎት እንዲተጋ መንፈሳዊ ጥሪ ቀርቧል፡፡
(በሳሙኤል ሀጎስ)